ሰላም እንዴት ከረማችሁ! ካሁን ቀደም አፄ ሚኒሊክ ከቅኝ ገዥ ወራሪ ሃይሎች ተከላክለውና መጨረሻ ላይም ከነዚሁ ቅኝ ገዥዎች ጋር ተደራድረው አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ እውን ካደረጓት ሃገረ- መንግስት ተፈጥረው፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ከተራቆተ ቤቱ ግብር እየከፈለ ባስገነባቸው ትምህርት-ቤቶች ተምረው ኣሁን አገሪቱን በማተራመስ ላይ ስለሚገኙት ቅጥረኞች እድሜ ልኬን ያየሁትን በሁለት ተከታታይ ርእሶች ለማጋራት ሞክሬ ነበር።
ኣሁንም ስለነዚህ ኣዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ተሰባስበው “ የትግራይ ምርጥ ዘር ነን” ብለው ፡ በተሓህት ስልቻ ተቋጥረው ፡ በደደቢት በረሃ ተዘርተው ፡ ዓሲምባ ስለበቀሉት ጉራማይሌዎች ዛሬም ከበርካታ በመንታ ምላሳቸው የተደሰኮሩት ውስጥ ጥቂቶቹን ላካፍላችሁ።
የአፄ ሃይለስላሴን ዙፋን የተቆናጠጠው ደርግ፡ አገሪቱን በሚያውቀው ወታደራዊ ቋንቋ፡ ‘ወደ ግራ ዙር’ ብሎ ፊቱን ወደ ምስራቁ ዓለም ጠመዘዘ። የምስራቁ ርእዮተ-ዓለምን ጠንቅቆ በመረዳት ሳይሆን፡ የዚያን ዘመን ፋሽን ስለነበረ ብቻ ሶሻሊስት ካባውን ተከናነበ። ወጣቱን፡ ብሎም የኢትዮጵያን ህዝብ ቀልብ ለመሳብ ይበጀኛል ያለውን እርምጃ ሁሉ ወሰደ።
ይሄኔ ነበር ስልጣኑን በወታደራዊ ሃይል የተቆጣጠረውን ወታደራዊ ስብስብ ለመቃወም እዚህም እዚያም የማያቋርጥ ሰላማዊ ሰልፍ መካሄድ የጀመረው። ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው ተቀዋሚ ድርጅቶች ብቅብቅ ማለት የጀመሩትም በዚሁ ግዜ ነበር። እንግድያውስ በዚህ አጋጣሚ ነበር የአያት ቅድመ-አያቶቹን ‘ወያናይ’ ኣስተሳሰቡን ደብቆ ሶስሻሊስት መፈክር አንግቦ ተሓህት ወደ ትጥቅ ትግል ያመራው።
የሶሻሊዝም ርእዮተ-ዓለም፡ ኋላ ላይ የተጋለጠውን ደካማ ጎኑን ትተን፡ ስለ መደብ ጭቆና፡ ስለ የሰው ልጆች እኩልነትና ፍትሃዊ የጋራ ተጠቃሚነት ወዘተ… ያስተምራል እንጂ ሰው ከሰው፡ ብሄር ከብሄር ይበልጣል ብሎ ኣይሰብክም። ተሓህቶች ግን የብሄር ማንነታቸውን ሰማይ ሰቅለው “አዮኹም ናይና” ፡ “ትግራይና ንቕድሚት” እያሉ የትግራይ ህዝብን ቀና አመለካከት ወደ ጥፋት አቅጣጫ መሩት።
አሜሪካ የምታራምደውን የምዕራቡን ዓለም አስተሳሰብ በነሱ ኣባባል “Imperialist Idiolojy” ለመታገል እንደተነሱ ለፈፉ። መች ይህ ብቻ፡ የሶሻሊስት ርእዮተ-ዓለም የሚከተሉትን ሶቭየትንና ቻይናን ‘አግላይ’’ { Revisionist } እያሉ በማንኳሰስ እነሱ ጥርት ያለ የአልባናውያንን ሶሻሊስት መስመር እንደሚከተሉ ነገሩን። የትግል ኣጋር ኣገኘሁ ብሎ ያቀፈውንና ወታደራዊ ልምዱን ያካፈለውን፡ ዓቅም በፈቀደ ሁሉ ትጥቅ ለግሶ ሱሪ ያስታጠቀውን ሻዖብያንም አግላይ ከሚላቸው ጎራ ፈረጀው።
ውድ አንባብያን ልብ በሉ! ትናንት “ምዕራባውያንን የሰውን ልጅ በህይወት እያለ ስጋውን በልተው አጥንቱን የሚቆረጥሙ ናቸው” በማለት ሰራዊታቸውንና ህዝባቸውን ያስተምሩ የነበሩት ተሓህቶች በአንድ በኩል፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተሓህትን የጎረምሶች ስብስብ፡ አሸባሪ ሽፍታ ይሉ የነበሩት አሜሪካኖች እንዴት አሁን አንዱ ታማኝ ተላላኪና ሌላው ጠበቃ ለመሆን በቁ? ‘በአንድ ራስ ሁለት ምላስ’ ይሏችኋል እንዲህ ነው።
አሜሪካውያን የነሱ ጥቅም አስፈጻሚ እስከሆነ ድረስ መንግስት አይሉ አሸባሪ ድጋፋቸውን ከመስጠት ወደ ኋላ እንደማይሉ በተደጋጋሚ ያየነውና የሰማነው ሃቅ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነውም ይህ ነው። ህዝባዊ መሰረት ያልነበረው ደርግ ውድቀቱ ሲቃረብ፡ አሜሪካውያን ጡረተኛ ፕረዚደንታቸውን ልከው እንሸምግላችሁ ብለው ነበር። ትናንት አሸባሪና ሽፍታ ይሏቸው ከነበሩት ድርጅቶች ጋር በክብ ጠረጴዛ ዙርያ ተቀምጠው ለድርድር ቅድመ-ዝግጅታቸውን ኣቀላጠፉት። የዋሆችና የአሜሪካ መንግስትን ባህሪ ላላወቁ የሰላም ሃዋርያት መስለው ቀረቡ።
የአቀራረባቸው ሚስጢር ግን በድርድሩ ወቅት ተተኪ ቅጥረኛ ለመመልመልና ለመለየት ነበር። ተሓህቶች ክፍት የስራ ቦታ በማግኘታቸው ፍቃደኛ ለመሆን ኣላንገራገሩም። በመሆኑም በህልም የከፈቱትን የአልባንያ ጽህፈትቤታቸውን ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ ጠንቅረው በመዝጋት ወደ ዋሽንግተን ዲሲ በረሩ። ወያኔ የአሜሪካን ትእዛዝ እስከፈጸመ ድረስ ሌላ የሚያሰጋው ሃይል እንደሌለ ኣረጋገጠ።
ይህን ተማምኖም የኢትዮጵያን ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ጨፈረበት። ትናንት ይሉት የነበረው ዳግም ላይነሳ ጭራሽ ተረሳ። ህዝብ ያልተቀበለው ህገ-መንግስት ጸድቆ ስራ ላይ ዋለ። ብሄሮች እስከ መገንጠል የሚደርስ መብት እንዳላቸው በአዲሱ ህገ-መንግስት ውስጥ ሰፈረ። የኢትዮጵያን ህዝብ ሃብትና ንብረት እንዳሻቸው ዘርፈው አልመች ሲላቸው ደግሞ የመገንጠል ህልማቸውን እውን ለማድረግ እንዲያስችላቸው፡ ያችኑ በኢትዮጵያ መልክኣ-ምድራዊ ካርታ የምትታወቀውን የትግራይ ክልልን፡ በአራቱም ማእዝኖች ከአጎራባች ክልሎችና ከጎረቤት ሃገር መሬት ቆራርሰው እየጨመሩ በአዲሱ የትግራይ ክልል ካርታ ላይ አሰፈሩ።
የኤርትራ መንግስት ጉዳዩን በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እዚህም እዛም ልኡካኑን ያሰማራ በነበረበት ግዜ ፡ የወያኔ ሚሊሽያ ባድመ አካባቢ ይንቀሳቀሱ በነበሩ የኤርትራ ሰራዊት አባላት ላይ ድንገተኛ ተኩስ በመክፈት ሶስት ወታደሮችን ገደሉ። በአካባቢው የነበረው የኤርትራ ሰራዊት በወያኔ ሚሊሽያ የተገደሉበት አባላቱን አስከሬን ለማንሳት ተኩስ የከፈተባቸውን የወያኔ ሚሊሽያ ማባረር ግድ ሆነበት።
በኢትዮጵያ ከዳር እስከ ዳር መንግስታዊ በትረ ስልጣኑን የተቆጣጠረው ወያኔ ፡ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማነሳሳት ‘ዳር ድንበራችን ተደፈረ’ ብሎ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አዳራሽና በመገናኛ ብዙሃን እሪታውን ለቀቀ። “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮህ” ነው ነገሩ። የወያኔ እሪታ ገዶት ሳይሆን ተገዶ ስፍር-ቁጥር የሌለው ሰራዊት በጦርነት ተማገደ።
ውድ ኣንባብያን ኣሁንም ልብ በሉ ! የኤርትራን የድንበር መንደር በጠራራ ጸሓይ ሰርቆ አዲሱ የትግራይ ካርታ ውስጥ የሰነቀረው ወያኔ፡ ተኩስ የከፈተው እሱ ራሱ ሆኖ እያለ ፡ ተወረረ የተባለው መሬት የትና የማን እንደሆነ የማያውቀውን ከመሃል ሃገር ያመጣውን ሰራዊት በጦርነት ወላፈን ውስጥ መማገዱን ምን ትሉታላችሁ? እርቃኑን የወጣው ወያኔ ሁላችንም እያየነው ስለሆነ መልሱን ለናንተው እተወዋለሁ።
በጦርነቱ ሂደት ስለነበረው አጠቃላይ ሁኔታ፡ ስለተቀጠፈው ህይወትና ስለነበረው የሃይል ሚዛንና ወታደራዊ ብቃት ከማንሳት መቆጠቡን መርጫለሁ። ምክንያቱም ቁስልን ፈውሶ ማዳን እንጂ፡ ነካክቶ ማባባስ ባህላችን የማይፈቅደው ነውር ነውና።
ይህ ሙከራ ውሃ እንዳልቋጠረላቸው የተገነዘቡት የወያኔ ጌቶች አሁንም ለሁለቱም ህዝቦች ተቆርቋሪ በመምሰል ጉዳዩ በዓለም-ኣቀፍ ህግ መሰረት ሁለቱም መንግስታት በሚቀበሏቸው ዳኞች አማካይነት በፍርድ ሂደት መቋጫ ይደረግለት የሚል አዲስ ሃሳብ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው በኩል ይዘው ከተፍ አሉ።
በድንበር ተሳቦ ሶስት መጠነ-ሰፊ የጦርነት ዘመቻ ሲካሄድና፡ የሺዎች ሰዎች ሂወት ሲቀጠፍ ፡ እድሜ ለዘመኑ ቲክኖሎጂ እንደ የሆሊዉድ ፊልም በሳተላይት ቲቪ ላይቭ ማለት በቀጥታ እየተመለከቱ ድዳቸውን ሲገለፍጡ እንዳልቆዩ ፡ ኋላ ላይ እንዴት ጉዳዩ በዓለም አቀፍ ህግ መቋጫ እንደሚያገኝ ትዝ ኣላቸው? እንዴትና ለምንስ ይሆን እሳቱን ለመለኮስ ክብሪት ሲያቀብሉ እንዳልነበር ኋላ ላይ ንዳዱን ለማጥፋት የተራወጡት? ዳግም “በኣንድ ራስ ሁለት ምላስ”። በነገራችን ላይ በዓለምኣቀፍ ህግ መሰረት የድንበር መንደሯ ባድመም ለኤርትራ ተወሰነች።
ይህን ጉዳይ በቅርበት ይከታተል የነበረው የወያኔው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፡ ውሳኔውን ሰምቶ የሃፍረት ካባውን ተከናንቦ ሳይውል ሳያድር አዲስ አበባ ገባ። ውሳኔው ለዓለም አቀፉ ማህብረሰብ በይፋ ሳይነገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋዜጠኖችን በመሰብሰብ ዓይኑን በጨው አጥቦ “ ባድመን ጨምሮ የጠየቅነውና ያልጠየቅነው መሬት ለኛ ተፈርዶልናል” የሚል መግለጫ ሰጠ። ሆኖም ውሸቱ በቀናት ውስጥ ነበር እራቅኑን የወጣው።
ፋኖና ቄሮ ተቀናጅተው ስልጣን ይብቃህ ብለው ወያኒን ኣላላውስ ኣሉት። በኢህኣዴጎች ውስጥ ሲያቆጠቁጥ የቆየው የለውጥ ሃይል በህጋዊ መንገድ ስልጣኑን እንደተረከበ፡ “የለውጥ አመራሮች የነበርነውም: ያለነውም: የምንመጣውም በፈጸምነውና በምንፈጽመው ወንጀል ተጠያቂዎች ነን፡ ህግ ከስልጣን በላይ ነው” ኣለ። ይህ የሃሰት የዘራፊዎችና የሌቦች ጥርቅም፡ በኢትዮጵያ ምድር የመቆየት ዕድሉ ማብቃቱን ሲያውቅ እደበቅባታለሁ ወዳላት ትግራይ ፈረጠጠ።
ከኒዚሁ ከፈረጠጡት የወያኔ ባለስልጣናት ውስጥ ለ 20 ዓመታት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረውና በመንታ ምላሱ የሚታወቀው አንዱ ነበር። የኢትዮ-ፎረም ጋዜጠኛ መቀሌ ድረስ በመሄድ ከዚህ ሰው ጋር ባደረገው ቃለ-መጠይቅ ካቀረበለት ጥያቄዎች ኣንዱ “ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ግዜ በዘ-ሄግ ይካሄድ የነበረውን የድንበር ግጭት ክርክርና የተሰጠውን ውሳኔ በቅርበት ይከታተሉ ነበር። ባድመን ጨምሮ ኣከራካሪ የነበረው የድንበር መሬት ለኤርትራ መንግስት መወሰኑን ከሰው በፊትና በላይ እያወቁ ከዘ-ሄግ ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሱ የፍርዱን ውጤት ለመገናኛ ብዙሃን ሲያብራሩ “ ባድመን ጨምሮ የጠየቅነውና ያልጠየቅነው መሬት በድንበራችን እንዲካለል ተወስኖልናል ብለው ነበር።
እንዲህ ያሉት ለምን ይሆን?” የሚል ነበር። ሰውየውም ሲመልስ፡ “ የህዝቡን ስነ-ልቦና ለመጠበቅ ዋሸሁ። ታድያ ሌላ ምን ትጠብቃለህ? በማለት ጥያቄውን በጥያቄ ነበር የመለሰለት። ኣሁንም ተጨማሪ ‘በአንድ ራስ ሁለት ምላስ!’
ኧረ ገና ይቀጥላል።
ውድ ኣንባብያን ለዛሬ እዚህ ላይ ይብቃኝ። ከመሰናበቴ በፊት ግን አንድ ማሳሰቢያ ጣል ባደርግ ደስ ይለኛል። ይህን አካባቢ ለማተራመስ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲል የቆየው ወያኔ መቃብር አፋፍ ላይ መሆኑን እያየን ነው። የሱ ጌቶች ግን ገና ፈርጣማ ክንዳቸውን ተገን አድርገው ተላላኪ ፍለጋቸውን እንደማያቋርጡ ተገንዝበን ጉያችንን ከተላላኪ ግለሰቦችና ድርጅቶች ማጽዳት ግዜው ይጠይቀናል። ጸንተን ከቆምን የአፍጋኒስታኑ ፍርጠጣ በአፍሪካም ይደገማል።
“ፈጣሪ ሰላም ፈላጊ ህዝባችንን ይጠብቅ”