የካቲት 11 ተገረመች!

0
68
TesfayeGebreabWeekly

ለ46 አመታት በወያኔ ቁጥጥር ስር የቆየችው የካቲት 11 በ2021 ነጻነቷን ተቀዳጀች። ከአረጋዊ በርሀ እስከ ደብረጽዮን የተቀያየሩት የህወሃት መሪዎች በየካቲት 11 ዋዜማ ዲስኩር በማሰማት በአሉን ሲያበስሩ ኖረው ነበር።

በነጋታው የካቲት 11 ሲሆንም፤ ከማለዳ እስከ ምሽት እንደ ጉድ ይታረዳል፣ እንደ ጉድ ይበላል፣ እንደ ጉድ ይጠጣል። “ጠላቶች” እንደ ጉድ የሚሞለጩበት እለትም ይችው የካቲት 11 ነበረች።

የ2021 የየካቲት 11 ዋዜማ ከመድረሱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ቃለመጠይቅ እንደሚሰጥ ተሰማ።

እለቱም የካቲት 10 ምሽት መሆኑ ሲነገር በቅድሚያ የተገረመችው የካቲት 11 እራሷ ነበረች።ምከንያቱም ደብረጺዮን የአይጥ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖም ቢሆን፣ በተለመደው የዋዜማው ምሽት መግለጫ እንደሚሰጥ ገምታ ነበር።

የአጋጣሚ ይሁን ታስቦበት መረጃ ባይኖርም፤ እንደ አድዋ፣ እንደ መቐለ፣ እንደ አክሱም፣ እንደ ሽሬ፣ እንደ አዲግራት የካቲት 11 የተባለችው እለትም ከወያኔ ቁጥጥር ነጻ ወጣች።

ርግጥ ነው፤ በየካቲት 11 ዋዜማ የወያኔ ትርፍራፊዎች አንድ ያልተገመተ ድርጊት ፈጽመዋል። ከተደበቁበት የአይጥ ዋሻ ሆነው መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ትግራይ የሚጓዘውን የኤሌክትሪክ መስመር ጎምደው በመጣል ትግራይን ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ጨመሯት።

የዚህ ድርጊት መልእክቱ ምንድነው?

የመጀመሪያው ግምታዊ መልእክት “አልሞትንም” የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛውም ግምታዊ መልእክት የትግራይ ህዝብ የፕሬዚዳንት ኢሳይያስን ቃለመጠይቅ እንዳይሰማ ለማገድ ሊሆን ይችላል።

ሁለቱም ደካማ ናቸው። በረሃ እያቋረጠ የሚሄድን የኤሌክትሪክ መስመር ማፈንዳት አንድ ግለሰብ ብቻውን ሊፈጽመው የሚችለው ነው። ስለዚህ ይህን በማድረግ “አልሞትንም” ማለት አይቻልም።

ባጭሩ ድርጊቱ የሽፍታ ስራ ነው።

“አልሞትንም” ለማለት የቀራቸው አቅም የኤሌክትሪክ ምሰሶ መፈንገል ብቻ ከሆነም፤ ወደ አዲስ አበባ የሚምዘገዘገውን መስመር መቁረጥ የበለጠ ትርጉም በሰጠ ነበር።

መከራው አላልቅ ያለውን ምስኪን የትግራይ ህዝብ ወፍጮ ቤት ማሳጣት ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም። የፕሬዚዳንቱን ቃለመጠይቅ ለማደናቀፍ ከሆነ በርግጥ ለአንድ ቀን ተሳክቶላቸዋል። ፕሬዚዳንቱ ስለ ደብረጽዮን እና መለስ ዜናዊ የተናገረውን የትግራይ ህዝብ ለዘለአለሙ እንዳይሰማ ማድረግ ግን የሚቻል አይደለም።

የካቲት 11 እንደ ሰው ልሳን አፍልቃ መናገር አትችልም እንጂ የመናገር እድል ብታገኝ ምናልባት በሰለለ ድምጽ እንዲህ ባለች ነበር፣ “ባልበላሁት እዳ ተጠላሁ። ለ46 አመታት ተጨፈረብኝ። ዛሬ ግን ነጻ ወጥቻለሁ። ወደ ሰላማዊዎቹ የየካቲት ቀናት በሰላም ተቀላቅያለሁ።”


“ለ46 አመታት ተጨፈረብኝ። ዛሬ ግን ነጻ ወጥቻለሁ። ወደ ሰላማዊዎቹ የየካቲት ቀናት በሰላም ተቀላቅያለሁ።””

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here