ሰላም አስተያየቴን በቅን ልቦና ለምትከታተሉ ወገኖች በሙሉ: አስተያየት ኣቅሪቢው የእድሜ ባለጸጋ ነኝ። ስልሳውን አጋምሼ ሰባኛውን እድሜየን ፈቅ በል በማለት ላይ እገኛለሁ። በግዕዝ ኣቆጣጠር በ1948 ይህችን ለሁላችንም ለሰው ልጆች በእኩልነት ልንኖርባት ተፈጥራ ግን በጥቂቶች ቁጥጥር ስር ያለችውን ዓለም ተቀላቀልኩ። በዚሁ እድሜየ ተባለ ተብሎ ስለሚወራና ሰዎች በስሜት የጻፉትን በማንበብ ሳይሆን ዕድሜ ልኬን ያየሁትንለ ማጋራት ካሁን በፊት ሞክሬ ነበር። አሁንም የዚሁን ተቀጥያ ለማካፈል ነው ብእሬን ያነሳሁት።
ካለኝ ዕድሜ የመጀመሪያዎቹን 18 ዓመታት ማለት 12ኛ ክፍል እስካጠናቅቅ የኃይለስላሴ መስፍናዊ አገዛዝ በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝብ ላይ ያወርድ የነበረውን አበሳ ከሞላ ጎደል ለማየት በቅቻለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ የመሳፍንቱን ፍላጎት በሟሟላት በአየር ፣ በባህርና በምድር ተንቀሳቃሽና ቋሚ መሳርያዎችን በመለገስ አይዞህ ፣ ርገጥ ፣ ጨፍልቅ ይሉት የነበሩት ባለውለታዎቹ አሜሪካና ተከታዮቿንም ታዝቤአልሁ። ምዕራባውያን ሃገራቸውን ተጠያቂነት በሚሸከሙ መንግስታት እያስተዳደሩ ለ42 ዓመታት ህዝቡን የረገጠውንv ኃይለስላሴን ግን እሽሩሩ ሲሉ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የለገሰላትን ለም መሬትና ውሃ ለመጠቀም ዘመናዊ የእርሻ መሳርያዎችን ከመለገስ ይልቅታንክና መድፍ በመለገስ እርስ በርሳችን ለመገዳደልና የኢትዮጵያ ህዝብ በረሃብ አለንጋ እየገረፈ እንዲኖር ፈረዱብን። በመንታ ምላስዋ የዲሞክራሲ ፈር ቀዳጅ ፣ የኢሰብአዊ ድርጊቶች ጠበቃ ነኝ እምትለው አሜሪካ እንዴት ከዚህ ከወድያኛው ዓለም ኢትዮጵያን ለመግዛት ከፈጣሪ የተላኩ ነኝ ክሚል ፍጡር ጋር ቃልኪዳን አሰረች የሚል ጥያቄ መንሳቱ የግድ ነው። ሚስጥሩ ከወዲህ ነው፤ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ማግስት የጣልያን ቅኝ ግዛቶች ነጻነታቸውን ሲያገኙ በአሜሪካ ግፊት ኤርትራ ለኃይለስላሴ በስጦታ መልክ ተበረከተች፣ ከዚያም አሜሪካ በወቅቱ ከአሜሪካ ግዛታዊ ክልል ውጪ ትልቁን ወታደራዊ መደበሯን በኤርትራ ምድር ከፈተች።
ዘግናኝ የወሎና የትግራይ የርሃብ እልቂት፣ በባላባቶችና በጭሰኞች መካከል የነበረው ኢፍትሃዊ የመሬት ኣጠቃቀም፣ መብቱን የጠየቀ ዜጋ በክብር ዘበኛ ሲረሸንና የተለያዩ በደሎች ሲፈጸሙበት: በኤርትራ ላይ ደግሞ “እምቢ ያለን ሰው ጥይት አጉርሰው” እየተዘመረ ሰው ባደባባይ ሲረሸን፣ ሲሰቀል፣ መንደሮች ሲቃጠሉና ህዝቡ ሃገሩን ጥሎ እግሩ ወደ መራው ሲሰደድ፣ የሰብአዊ መብት ጠበቃዋ አሜሪካና ግብረኣበሮችዋ የት ነበሩ?
ከ1961-1991 ለ30 ዓመታት የኤርትራ ህዝብ ለነጻነቱ ሲዋደቅ የኢትዮጵያ ሰራዊትን በትርክቶች አታለው ወደእሳት በመማገድ የውጭ ሃይሎች ተላላኪና ኣጎብዳጅ ለነበሩት ስርዓቶች ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሲዋደቁ ዓይናቸው አላይ ጀሮአቸው አልሰማ ብሎ ቆየ።
በ1991 እንዴትና በምን ተአምር ነው የታወሩት ዓይኖች የተከፈቱት መስማት የተሳናቸው ጆሮዎች መስማትv ጀምረው “በዓለም ኣቀፍ” ህግ መሰረት ጉዳዩን ለመቋጨት ሽርጉድ የተባለው? መቼ ይህ ብቻ የኤርትራ ህዝብ ነጻነቱን ተቀዳጅቶ ገና 8 ዓመት ባልሞላ ዕድሜው ለሃገሩና ለህዝቡ ባልቆመ ተላላኪው ወያነ በድንበር አሳበው ጦሩነት ከፈቱበት።
የኤርትራ ህዝብና መንግስት ነጻነቴን ላጣጥም እጃቹሁን ሰብስቡ፣ ተፈጥሮ የለገሰንን ምድርና ባህር ለኛ በሚበጅ መንገድ እንጠቀምበት፣ በድንበራችን ውስጥ እኛንም ሆነ ጎረቤት ህዝቦችን የሚጎዳ ቅንጣት መሬት አናላከራይም ስላለ ብቻ በወኪሉ ወያኔ ዳግም ጦርነት ተከፈተበት።
3 መጠነ ሰፊ ዘመቻዎች በአሜሪካ የሳተላይት ቴክኖሎጂና የመረጃ ቅብብሎሽ እየተመራ ኤርትራን ለመደምሰስ አለያም ለማንበርክ በተደረጉት ውጊያዎች ከ120,000 በላይ ኢትዮጵያውያንን አስቀጠፉ። ያሰቡት ሳይሳካ ሲቀር በድጋሚ ብዥ ላለው ዓይናቸው መነጸር: መስማት ለተሳነው ጀሮቸው ኢርፎን (earphone) ያገኙ ይመስል ለሽምግልና ተራወጡ። ጦርነት ለማስጀመር ቡራኬ ሰጥተው የሚያስጀምሩት እነሱ አልሆን ሲላቸው ለሽምግልና የሚራወጡት እነሱ ሁነው የሚቀጥሉት እስከ መቼ ነው ?
በዓለም አቀፍ ፍርድቤት ውሳኔ ያገኘውን የድንበር ጉዳይ ማስፈጸም ላይ ተላላኪያቸው ምክንያት እየፈጠረ ሲያጓትተው አንድም ቀን ስለ ማዕቀብ አስበውና አውርተው የማያቁት የወያኔ ጌቶች: የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንዳለ የተቀበለውን የኤርትራ መንግስት ላይ ግን ቁጥር ስፍር የሌለው ማዕቀቦች ሲያደርጉ ቆይትዋል ኣሁንም ቀጥለዋል።
ውድ አንባብያን ልብ በሉ፤ ኃይለስላሴ ለ42 ዓመታት፣ ደርግ ለ17 ዓመታት፣ ወያኔ ደግሞ ለ27 ዓመታት አንድም ሁለትም ሃገር ሆነው የኖሩና ያሉ ህዝቦችን ሲረግጡና ደም ሲያቃቡ የነበሩት ስርዓቶች ላይ ማዕቀብ እሚባለው በትራቸው ሰንዝረው ያማያውቁ ምዕራባውያን አሁን ኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ ካሉት መንግስታት በላይ ለሁለቱም ህዝቦች ተቆርቋሪ ሆነው ለመገኘት ላይ ታች ሲሉ ማየት ምን ያህል ንቀት እንዳላቸው ለማወቅ አያዳግትም። እኛ ኤርትራውያን ማዕቀብ (sanction) እሚለው ቃል በነሱ ቋንቋ Hi and Bye ከሚለው ተራ ቋንቋ ለይተን ከማናየው ዓመታት አስቆጥረናል።
ኢትዮጵያዊያንም ምንም እንኳን አዲስ ቢሆንባቸውም ልምዱን በመካፈል ላይ ናቸው። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ታሪክ የኢትዮጵያ ህዝብ ካለፈው በተሻለና በበለጠ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተወዳድረው መንግስት ስለኣቋቋሙ፣ ተወዳድሮ ስልጣኑን የተቆጣጠረ ፓርቲም ታይቶና ተስምቶ ብማያቅ ሁኔታ መንግስታዊ ስልጣኑን ለተፎካክሪ ፓርቲዎች ስላጋራ፣ ከታንክና መድፍ ቁጥር በላይ ትራክተርና ኮምባይነር ስላስገባ፣ ከስንዴ ልመና ለመላቀቅ ተፈጥሮ የለገሰለትን መሬት ውሃና ጉልበት ዘመኑን በሚመጥን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ህዝቡን ከድህነትለማውጣት በመሞኮሩ፣ የሃገሩን ሰላም ከአጎራቧች ህዝቦች ሰላም ጋር በማስተሳሰር እውነተኛውን የሰላምመንገድ በመጥረጉና ሌላም ሌላም ብዙ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅም ስራዎች በማከናወኑ ማዕቀብና በደረሱበት ቴክኖሎጂ የተቀናጀ የፕሮፖጋንዳ ውግያ በማድረግ ህዝባዊውን መንግስት ጥለው ዘረኛና ተላላኪውን ወያኔ ለማምጣት ቃጣቸው?
ሚስጥሩን ፈትሾ ለማውጣት በቅን ልቦና ለኢትዮጵያዊነታቸው ለሚዋደቁ ወንድሞቼ እተወዋለሁ። አደራ እምለው ግን ችግሩን ለመግጠም የብሄር ማንነትንና የበላይነትን በመርሳት ብአንዲት ኢትዮጵያ አምናችሁ በጥናት ከቆማችሁ ችግሩን ላንዴና ለመጨረሻ ፈታችሁ ብርሃን አመንጭቶ ድንበር ዘሎ ከሚፈሰው ጎርፍ ጋር ችግር ለመፍጠር እንቅልፍ ወደ ኣጡት እንደምትልኩት እርግጠኛ ሆኜ ለመተንበይ እችላለሁ።
በዚህ አጋጣሚ አንዳንድ በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎችና የቀድሞው የሰራዊቱ አመራር የነበሩ ግለሰቦች በ1998 በወያኔ ተላላኪነት የተካሄደውን ጦርነት የኢትዮ – ኤርትራ ጦርነት እያሉ ይደጋግሙታል። ጦርነቱ ግን ወያኔ ከጌቶቹ ትእዛዝ ተቀብሎ ኤርትራን ለመደምሰስ አለያም ለማዳከም የከፈተው ጦርነትና: በጦርነቱም ይሁን በፍርድ ቤት በወያኔ ተሸናፊነት መቋጫ ያገኘ ስለሆነ ወይኖ – ኤርትራ ብትሉት ይበጃል። ምክንያቱም በኢትዮጵያውያ የነበረው ስርዕት የኢትዮጵያውያንን ፍላጎት ሳይሁን የስስታሙንና የተላልኪውን ወያኔ ፍላጉት የሚያስፈጽም መንግስታዊ መዋቅር ስለነበረ።
ሌላው መታረም ያለበት መግለጫ ወያኔ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ላይ የከፈተውን ጦርነት በተወሰኑ ክልሎችና ብሄሮች ላይ ጦርነት እንደከፈተ የሚያሰማ መግለጫ በተደጋጋሚ ይስራጫል። ወያኔ ከተቀበረበት ጉድጓድ ወጥቶ አዲስ አበባ ለመግባት በአየር በሮ አይሄድም። አጎራባች ክልሎችን በሃይል አንበርክኮ ለማለፍ ግን ይሞክራል። በዚህ አጋጣሚ በውግያው ዞን ያለው ህዝብና ንብረት የጦርነቱ ገፈጥ ቀማሽ መሆኑ አይቀሬ ነው። ከዚህ ጥራዝ ነጠቅ የወያኔ ፓለቲካ መማርና እሱ የፈጸማቸው ጉድለቶች እንዳይደገሙ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
ወያኔ ”ታላቋን ትግራይ” የመመስረት ህልሙን ለማሳካት አዲስ የትግራይ ካርታ ሲሰራ በአራቱም መእዘናት ምን ያህል መሬት መውረሩን የማያውቅ ኢትዮጵያዊ የለም። በተለይ በኤርትራ ወሮ የያዘውን መሬት ኤርትራ እንደመንግስት በህጋዊ መንገድ ስትጠይቅ ወያኔ በድንበር ጥበቃ ላይ በነበሩ የኤርትራ ሰራዊት አባላት ላይ ተኩስ በመክፈት ጦርነቱን ጫረ።
ያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ ሃብትና ሰብኣዊ ጉልበትን ለመጠቀም: በወረራ ወደ ትግራይ ክልል ያካተትነው መሬት እየተወልሰደብኝ ነው ከማለት ይልቅ፤ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ተደፈረ ብሎ ኢትዮጵያውያንን በስሜት ቀስቅሶ በእሳ እንዳስፈጃቸው የቅርብ ግዜ ትዝታ ነው።
በአንጻሩ አሁን እየተካሄደ ያለው ጦርነት ግን የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት በሚከላከሉና አንድነትዋን ለመበታተንና ከ80 በላይ ብሄሮች የእርስ በእርስ ህልቂት ውስጥ አስግብቶ ከጌቶቻቸው ጋር ዳር ቆመው ለመሳቅና ለመሳለቅ የደረሱት ድራማ መሆኑን ልብ ማለት ግድ ይላል።
ስለዚህ አማራን፡ አፋርን ለማጥፋት የሚባለውን ትርክት ትታችሁ በአንዲት ኢትዮጵያ ላይ እንደተቃጣ ጦርነት ወስዳችሁ ጡሩነቱን መፋለም ይመረጣል።
ሌላው ኣስደሳች ዜና በህዝቦች መካከል ያለው ትስስርና እምቢ ለአስመሳይዋ ዲሞክራት አሜሪካና ግብረኣበረችዋ የሚል መፈክር እዚህም እዛም በየቀኑ ሲስተጋባ ይሰማል። በተለይ ሃገር ወዳደ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ዲያስፓራ እሰየው እንኳን ለዚህ አበቃን የሚያሰኝ እንቅስቃሴ በጥምር እየታየ ነው።
ይህን አመለካከት ከሌሎች አፍሪካውያን ጋር በመጋራት ዲያስፓራው በያለበት ሃገር ድምጹን በአንድ ላይ ለማሰማት መነሳሳት ግዜው አሁን ነው። ምክንያቱም ሁላችንም የሰው ልጆች ከ9 ወር በእናቶቻችን ማህጸን ቆይታ በኋላ ለሁላችንም ከ5 ህዋሳተ ኣካልት (sense organs) ጋር እንደተፈጠርን ብዙ ሳይንሳዊ ምርምር የማያስፈልገው እውነታ ስለሆነ። ታድያ ለምን ይሆን ሃገሮቻችንን በነጻነት እኛ በመረጥነው መንገድ ለማስተዳደር የሚነግፉን? እስከ መቼ ነውስ የኛ የጥቁር ህዝቦች አእምሮና ጉልበት ፈሶበት በተሰራው የሳተላይት ቴክኖሎጂ እኛን ከሩቅ በሪሞት ኮንትሮል (remote control) ለማስተዳደር ሲሞክሩ ዝም ብለን የምናየው? ሌላም ሌላምብዙ ለምን? እንዴት? እስከመቼስ ነው አሜሪካና ግብረአበሮችዋ በኛ በጥቁር ህዝቦች ዋጋ አለሁ አለሁ የምትለው?
በመጨረሻ ግን አለን ብለው በሚመጻደቁበት ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የመሰብሰብና ሓሳብን በነጻ የመግለጽ አስመሳይ ዲሞክራሲያቸውን ተጠቅማችሁ ኢትዮ – ኤርትራ ዲያስፖራዎችና ሌሉች መሰል አፍሪካውያንንበማስተባበር አሜሪካንና ግብረአበሮችዋን “ይብቃችሁ እጅ እግራችሁን ስብስቡልን #NoMore!“ ማለቱ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
ሃገር ውስጥ ያለነውም ለተንኮለኛ ሴራችሁ “ወይ ፍንክች” ማለቱን አጠናክረን እንቀጥላለን። በአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ ሃገራት ብሎም አፍሪካውያን ለእድገታችንና ለብልጽግናችን ማነቆ የሁነውን የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት ለማስወገድ እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደ ፊት እምንልበት ጊዜ አሁን ነው። ካልሆነ ግን እጣ ፈንታችን የሶርያ፣ ኢራቅ፣ ሊቢያ አፍጋኒስታን ወዘት እንደሚሆን መገንዘብ አለብን ።
ድል ለስፊው ህዝብ !!
ፈጣሪ ሰላማችንን ይጠብቅ !!